አስደሳች ዜና

የዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የስፖርት ጂምናዚየም ለሰራተኞቹና ለከተማው ማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ሰኔ 01/2018 ዓ.ም

‎የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎቹ፣ ለሰራተኞቹ እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰጠውን ሁለንተናዊ አገልግሎት ይበልጥ ለማሳደግ ታስቦ የተደራጀው የስፖርት ጂምናዚየም ማዕከል አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን አሟልቶ በዛሬው ዕለት በይፋ ስራ ጀምሯል።

‎ማዕከሉ በይፋ ስራ መጀመሩን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው ባደረጉት ንግግር ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር አዕምሮው የጎለበተ ትውልድን ብቻ ሳይሆን የተሟላ ስብዕና ያለው እና ጤንነቱ የተጠበቀ፤ በአካልም የጎለበተ ትውልድን ለመፍጠር ጂምናዚየሙ ስራ መጀመሩ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

‎በማዕከሉ ለስፖርቱ ቅርበት ያላቸው አካላት ብቻ ሳይሆን ሌላው የግቢውም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የስፖርት ባህል እንዲዳብር የተጀመሩትን በማስቀጠልና በማጠናከር ሁሉም በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

‎የአስተዳደርና ቢዝነስ ልማት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር በላይ መንግስቴ በበኩላቸው ስፖርት በአዕምሮ፣ በአካልም ሆነ በስነ-ልቦና የጎለበተ እንዲሆን የሚያደርግ በመሆኑ ይህንን ጂምናዚየም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠብቆና ተንከባክቦ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

‎የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደርበው ንጉሴ ማዕከሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የስፖርት ቁሳቁሶች የተሟሉለት በመሆኑ የመማር ማስተማር ሂደቱ ከንድፈ-ሃሳብ በተጨማሪ በተግባር የተደገፈ ጥራት ያለው ትምህርትን ከመስጠት ባለፈ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የታገዘ የተለያዩ የአካል ብቃት ስልጠናዎችን ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

‎በማዕከሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የደም ግፊትና የስኳር መጠንን መለካት፣ በማሽን የታገዘ ማሳጅ፣ በባለሙያ የታገዘ የማማከርና ሌሎች መሰል አገልግሎቶች እንደሚሰጡ የገለጹት የስፖርት ሳይንስ ት/ት ክፍል ኃላፊ መምህር የሸዋስ ጀምበሩ ናቸው።

መ/ር የሸዋስ አክለውም ማንኛውም የግቢውም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ ወደ ማዕከሉ በመምጣት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንድትሆኑ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

‎በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ማዕከሉን የጎበኙ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊ እንግዶች በሰጡት አስተያየት በማዕከሉ መከፈት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

‎ዘገባው የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ነው።

‹‹አእምሮ ሲከፈት፤ ዓይኖች ማየት ይችላሉ›› ‹‹ Open Mind, Open Eyes!››
የተቋሙን ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፤
Web site: https://wldu.edu.et/
Facebook : https://www.facebook.com/WoldiaUniversity
Telegram Channel:  https://t.me/Woldia_University
YouTube:  https://www.youtube.com/channel/UCHt88As5v2BmynWine1Oexw
P.O.Box = 400
Woldia Town, Amhara Region, Ethiopia.

Leave a Reply