
የካቲት 03/2018ዓ.ም (የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት)
ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ያሰራው የህጻናት ማቆያ ማእከል በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
በማእከሉ ምረቃ መርሀ-ግብር ላይ የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል የተከበሩ አቶ ዱባለ አብራሬን ጨምሮ ከዞንና ከከተማ የተጋበዙ የስራ ሀላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እና ወላጆች ተገኝተዋል።
የህጻናት ማቆያ ማእከሉን ሪቫን በመቁረጥ በይፋ ስራ ያስጀመሩት የተከበሩ አቶ ዱባለ አብራሬ እና ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር አበበ ግርማ ሲሆኑ፤ ተጋባዥ እንግዶችም ማእከሉ የሚሰጠውን አገልግሎትና አጠቃላይ ስራውን ጎብኝተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር አበበ ግርማ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ዛሬ በይፋ ስራ የጀመረው የህጻናት ማእከል ዘመኑን የዋጀ የህጻናትን አእምሮአዊና አካላዊ እድገትን ሊያግዝ የሚችል መንገድ ታቅዶና በሁሉም ቀና ትብብር የተሰራ ማእከል መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ልጆች የወልድያን፣ የሰሜን ወሎን ብሎም የወሎን ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን እንዲያውቁ በማድረግ እንደሀገር የሚያስቡ እንደ አለም የሚፈጽሙ ልጆች እናገኝበታለን ብለዋል።
ግንባታውን በተመለከተ በርካታ ልምድ ልውውጥ ተወስዶ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ያወጣውን የህጻናት ማቆያ ግንባታ ስታንዳርድ መሠረት በማድረግ በቋሚነት ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን አቅደን ነው የሰራነው ሲሉ ተደምጠዋል። ዛሬ ተመርቆ በይፋ ስራ የጀመረው የህጻናት ማቆያ ማእከል ለብዙ ተቋማት ምሳሌ ከመሆኑም በተጨማሪ የተቋሙ ሴት ሰራተኞች በልጅ ማሳደግ ምክንያት ከስራ ገበታቸው እንዳይሰናከሉ ያደርጋል።
በዚህ ደረጃውን በጠበቀ ማእከል እየዋሉ ለሚያድጉ ህጻናት ለሀገር የሚኖራቸው ፋይዳ የጎላ ነው ያሉት የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል የተከበሩ አቶ ዱባለ አብራሬ ናቸው። ክቡር ከንቲባው አክለውም ይህ ፕሮጀክት የቅንጦት አይደለም ያሉት ከንቲባው ለነገ ሀገርን ለመሥራት ዛሬ አስበን የምንሰራው አስፈላጊ ተግባር ነው ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ብርቱካን ወዳጅነው በበኩላቸው የስራ ክፍላቸው እንዲተገብሯቸው በመንግስት ሀላፊነት ከተሰጣቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ ደረጃውን የጠበቀ የህጻናት ማቆያ ማእከል በተቋሙ እንዲኖር ማድረግና ማእከሉን ማስተዳደር መሆኑን ጠቁመዋል። አክለውም ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የተባበሩ አካላትን በሙሉ በስራ ክፍላቸው ስም አመስግነዋል።
ማእከሉ የሴት ሰራተኞችን በስራ ላይ ውጤታማ ከማድረጉም በተጨማሪ ለህጻናት እድገት መሰረታዊ በሚባለው ከ6 ወር እስከ አራት አመት እድሜ ውስጥ ማግኘት ያለባቸውን እንክብካቤ እንዲያገኙ ያደርጋል። ለዚህም ተብሎ የግድግዳ ስእሎችና ቀለሞች ሲቀቡ የህጻናትን እድገት በበጎ ሊቀርጹ በሚችሉ ሀገራዊ ይዘቶችንና ታሪካዊ ቦታዎችን ጭምር ያካተተ ተደርጎ ነው ተሰራው።
ማእከሉ በውስጡ የመኝታ፣ የመመገቢያ፣ መጫዎቻ፣ የናቶች ጡት ማጥቢያ፣ የነርስና የሰራተኞች ክፍል፣ በመጸዳጃ ክፍሎች የተማሉለት ሲሆን ሁሉም አይነት ግብአቶች የህጻናትን እድሜ ባገናዘበ መልኩ ደጀቻቸውን የጠበቁ እንደሆኑ በጉብንት በርሀ-ግብሩ ላይ ተገልጿል።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የህጻናት ማቆያ በአሁኑ ሰአት 60 ህጻናትን እያስተናገደ ሲሆን፤ የሰራተኞችን ፍላጎት ለማሟላት በቀጣይ የህጻናትን ቁጥር ለመጨመር እና ወደ ቅድመ መደበኛ ት/ት ቤት (Kindergarten/ KG) ለማሳደግ እቅድ እንዳላቸው ወ/ሮ ብርቱካን ጠቁመዋል።
‹‹አእምሮ ሲከፈት፤ ዓይኖች ማየት ይችላሉ›› ‹‹ Open Mind, Open Eyes!››
የተቋሙን ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፤
Web site: https://wldu.edu.et/
Facebook : https://www.facebook.com/WoldiaUniversity
Telegram Channel: https://t.me/Woldia_University
YouTube: https://www.youtube.com/channel/UCHt88As5v2BmynWine1Oexw
P.O.Box = 400
Woldia Town, Amhara Region, Ethiopia.