
ጥር 28፣ 2018ዓ.ም (የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት) በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ የቴክኖሎጅ ሸግግርና ማህበረሰብ አገልገሎት ፅ/ቤት የምርምር፣ህትመት፣ስነ-ምግባርና ስርዓት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የተጠናቀቁ ሁለት የምርምር ጆርናሎችን በይፋ የምስረታ ፕሮግራም በማዘጋጀት በዛሬው ዕለት አስተዋውቋል። በፕሮግራሙ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር አበበ ግርማ፣ የአሰተዳደርና ቢዝነስ ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር በላይ መንግስቴን ጨምሮ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ስራ አስፈፃሚዎችና የሚመለከታቸው ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል። በፕሮግራሙ መክፈቻ ዕለት ንግግር ያደረጉት ዶ/ር አበበ ግርማ “ከብዙ ጥረት በኋላ ዩኒቨርሲቲያችን የእውቀት አድማሱን የሚያሰፋበትና ለአለማቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ የምንሆንበትን አዲስ ምዕራፍ በመጀመራችን እንኳን ደስአላችሁ ብለዋል።” ፕሬዝደንቱ በዛሬው ዕለት ያስጀመርናቸው ሁለቱ የላሊበላ የማህበራዊ ሳይንስ እና ሂውማኒቲስ መፅሔት (Lalibela Journal of Social Science and Humanities-LJSSH እንዲሁም የላሊበላ የግብርና እና ተግባራዊ ሳይንስ መጽሔቶች (Lalibela Journal of Agricultural and Applied Sciences- LJAAS ) የእውቀት መፍለቂያ፣ የሳይንሳዊ ግኝቶች ማከማቻና መሰራጫ፣ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽነታችንን የሚያሰፉ በመሆናቸው በትኩረት ሊሰሩባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል። አያይዘውም መድረኮቹ የልህቀት ማሳያዎች በመሆናቸው የአካባቢያችንን ችግሮች የሚፈቱ፣ የዓለም አቀፍ ጥያቄዎችን የሚመልሱና ጥናቶች ለንባብ የሚበቁባቸው እንዲሆኑ ሙህራን ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበው ለውጤቱ መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል። የጆርናሎቹን ምስረታ መነሻ በማድረግ አጭር ገለፃ ያደረጉት የምርምር፣ ህትመት፣ ስነ-ምግባርና ስርዓት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር እንዳልካቸው ፈቃዱ እንደገለፁት ጆርናሎቹ እውቀትንና ግኝቶችን በማከማቸት፣ በማደራጀት ለሀገርአቀፍና አለምአቀፍ ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ፣ የተመራማሪዎቻችን ድካምና ውጤት ለማሳየት፣ በሳይንሳዊ መድረኮች ዘንድ ድምፃችን የሚሰማበት እድል ለመፍጠር ይህንን ትልቅ መሰረት ጥለናል ብለዋል። አክለውም የጆርናሎቹን አቅምና ጥራት በማሳደግ ሙህራን የምርምር ውጤቶቻቸውን በማሳተም፣ በአርትኦትና በግምገማ ሂደቱ በንቃት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። የአሰተዳደርና ቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር በላይ መንግስቴ በበኩላቸው የጆርናሎቹ ስራ መጀመር አለም አቀፍ እውቅናን ለመፍጠር፣ የምርምር ፕሮጀክቶችን ለማግኘት፣ አጋርነትን ለማሳደግና የተቋሙን መልካም ገፅታ ለመገንባት የጎላ ፋይዳ ስላለው ጥራት ያላቸውን ስራዎች መስራት አንደሚገባ ተናግረዋል። በፕሮግራሙ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የቀረበውን አጭር ገለፃ መሠረት በማድረግ ገንቢ የሆኑ አስተያየቶችን ሰጥተው በቀጣይ ሌሎች የሙያ መስኮችም በአርኣያነት ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።
‹‹አእምሮ ሲከፈት፤ ዓይኖች ማየት ይችላሉ›› ‹‹ Open Mind, Open Eyes!››
የተቋሙን ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፤
Web site: https://wldu.edu.et/
Facebook : https://www.facebook.com/WoldiaUniversity
Telegram Channel: https://t.me/Woldia_University
YouTube: https://www.youtube.com/channel/UCHt88As5v2BmynWine1Oexw
P.O.Box = 400
Woldia Town, Amhara Region, Ethiopia.