
መስከረም 26/2018 ዓ.ም (የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት)
የሰሜን ወሎና ወልድያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ተኮር ኤፍ ኤም 89.2 ሬዲዮ ጣቢያ 2ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ/ር) ሬዲዮ ጣቢያው የማህበረሰቡን ተሳትፎና የተቋሙን ተግባራት የሚያገናኝ ትልቅ ድልድይ ነው ብለዋል።
የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህልና ወግ ለሌሎች በማስተዋወቅ ረገድ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ የመረጃ ማሰራጫ የማህበረሰብ አገልጋይ ጣቢያ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላላ ጉባዔው በወቅቱ እየተገናኘ ድክመቱንና ጥንካሬውን መገምገሙና የቦርድ አባላት ምርጫን ማካሄዱ የተደራሽ አድማሱን በማስፋት ጥራት ያለውና ተዓማኒ መረጃዎችን ለአድማጭ ማህበረሰቡ ለማድረስ ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አክለው ገልጸዋል።
በ2011 ዓ.ም በአንድ ኪሎ ዋት የሬዲዮ ጣቢያ ትራንስሚተር ጉልበት በ150 ኪሎ ሜትር ራዲየስ በቀን ለ5:30 ያክል መደበኛ የስርጭት ስራውን በጦርነት ውድመት እስከደረሰበት እስከ 2013 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት የራዲዮ ጣቢያው ስራ አስኪያጅ አቶ ኪዳነማሪያም ጌታሁን ናቸው።
ከደረሰበት ውድመት በኋላ በአዲስ መልክ ተቋቁሞ በ2016 ዓ.ም ዳግም መደበኛ የስርጭት ስራውን ጀምሮ በሶስት ኪሎ ዋት ከወልድያ በ150 ኪሎ ሜትር ራዲየስ፤ ከላሊበላ መቀባበያ ጣቢያ ደግሞ ከ150 እስከ 200 ኪሎ ሜትር ራዲየስ በሚደርስ በቀን ለ7:00 ያክል በ16 የተለያዩ ፕሮግራሞች አስተማሪ፣ አዝናኝና መረጃ ሰጭነት ላይ ተመርኩዞ በሰሜን ወሎ ዞንና ሌሎች አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ተደራሽ በመሆን የስርጭት አድማሱን አስፍቶ እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ኪዳነማሪያም አያይዘው ተናግረዋል።
ተሳታፊዎች በበኩላቸው በስራ አስኪያጁ አቶ ኪዳነማሪያም ጌታሁን የቀረበውን የሬዲዮ ጣቢያው ሪፖርትን መሰረት በማድረግ በርካታ ሃሳብ አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን በአወያዮች አማካኝነት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ጠቅላላ ጉባዔው ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ ከተማሪዎች ህብረት ተወካይና ከግቢው ውጭ ከሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያካተተ ሰባት ተወካዮችን የቦርድ አባላት በማድረግ መርጧል።
በየሶስት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግና የቦርድ አባላት ምርጫን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ በሚደነግገው የብሮድካስት ባለስልጣን ህግ መሰረት የተካሄደ የጠቅላላ ጉባዔና የቦርድ አባላት ምርጫ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አቶ ኪዳነማሪያም ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲውን ጨምሮ ከወልድያ ከተማ አስተዳደርና ሰሜን ወሎ ዞን እና ወልድያ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የዩኒቨርሲቲው አካላት በተካሄደው 2ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝተዋል።
‹‹አእምሮ ሲከፈት፤ ዓይኖች ማየት ይችላሉ›› ‹‹ Open Mind, Open Eyes!››
የተቋሙን ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፤
Web site: https://wldu.edu.et/
Facebook : https://www.facebook.com/WoldiaUniversity
Telegram Channel: https://t.me/Woldia_University
YouTube: https://www.youtube.com/channel/UCHt88As5v2BmynWine1Oexw
P.O.Box = 400
Woldia Town, Amhara Region, Ethiopia.